ኦፊርዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን የሚጠቀስ አገር ነው። በኦሪት ዘፍጥረት 10 የኖህ ልጆች ሲዘረዘሩ ከዮቅጣን ልጆች መካከል አንዱ ኦፊር የሚባል አለ።

መጽሐፈ ነገሥታት ቀዳማዊ 9፡26-28 መሠረት፣ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን መርከበኞች ከዔጽዮንጋብር ወደብ በኤርትራ ባህር (ቀይ ባህር) በመጓዝ ወደ ኦፊር መጥተው ከዚያ 420 መክሊት ወርቅ ወደ ሰሎሞን አመጡ። (በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ እንደገና 450 መክሊት አመጡ።) በምዕራፍ 10፡11 እነኚህም መርከበኞች ብዙ የሰንደል ዕንጨትና ዕንቁ ከኦፊር አመጡለት። እንዲሁም በምዕራፍ 22፡48 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ «ወደ ኦፊር ሄደው ወርቅ ያመጡ ዘንድ የተርሴስን መርከቦች ሠራ፤ ነገር ግን መርከቦቹ በዔጽዮንጋብር ተሰበሩ እንጂ አልሄዱም» ይለናል። ከዚህ በላይ «የኦፊር ወርቅ» በመጽሐፈ ዜና መወዕል ቀዳማዊ 29፡4፣ በመጽሐፈ ኢዮብ 22፡24፣ 28፡16፣ በመዝሙረ ዳዊት 45፡9 እና በትንቢተ ኢሳይያስ 13፡12 ይጠቀሳል።

ስለ ዮቅጣን 3 ልጆች ስለ ሳባ፣ ኦፊርና ኤውላጥ የሆነ ተጨማሪ መረጃ በአንዳንድ ጥንታዊ የአረብኛ፣ የሱርስጥ ወይም የግዕዝ ጽሑፍ ተገኝቷል።

  • ኪታብ አል-ማጋል የሚለው በራግው ቀኖች የሳባ ንጉሥ «ፈርዖን» ኦፊርንና ኤውላጥን ለመንግሥቱ ጨመረ፣ ከዚያ «ኦፊርን ከወርቅ ድንጋይ ሠራ፤ የተራሮቹ ድንጋዮች ጥሩ ወርቅ ናቸውና»።
  • የመዝገቦች ዋሻ እንዲህ አለው፦ «የኦፊርም ማለት የስንድ ልጆች ንጉሣቸው እንዲሆን ሎፎሮን ሾሙ፤ እሱም ኦፊርን ከወርቅ ድንጋይ ሠራ። አሁን በኦፊር ያሉት ድንጋዮች ሁሉ የወርቅ ናቸው።»
  • የአዳምና የሕይዋን ትግል ከሠይጣን ጋራ እንዲህ ይተርከዋል፦ «ፋርአን በሳፊር (ኦፊር) ልጆች ላይ ነገሠ፤ እርሱም የሳፊርን ከተማ ከወርቅ ድንጋዮች ሠራ፤ ያውም የሳራኒያ አገር ነው፤ ስለነዚህም ወርቅ ድንጋዮች፣ የዚያው አገር ተራሮችና ድንጋዮቹ ሁሉ የወርቅ እንደ ሆኑ ይላሉ።»

የኦፊር ሥፍራ እርግጥኛ አይደለም። ምክንያቱም ነገደ ኦፊር በያፌት፣ በሴምና በመጨረሻ በካም ልጆች መካከል እንደ ተገኙ የሚሉ መዝገቦች አሉ። መጀመርያ አቬንቲኑስ እንደሚጽፍ፣ ነገደ ኦፊርና አንዳንድ ሌላ የዮቅጣን ሕዝብ በባልካኖች ገብተው ኦፊር በኤፒሩስ የዛሬው አልባኒያ ሠፈሩ። ሌሎች ጽሑፎችም እንደ ሜቶዲዮስ እንደመሰከሩ ከትንሽ ዘመን ቀጥሎ ነገደ ኦፊር በአውሮፓ መቆየት ስላልወደዱ ወደ ኢንዱስ ወንዝ ሸለቆ ተጓዙ። በሌሎች ምንጮች «ፑሩ» እና «ሜሉሓ» የሚባለው አገር ነበር። ሃይሮኒሞስና ሌሎች ደግሞ እንደጻፉ፣ ከጥቂት መቶ ዓመት በኋላ ከኢንዱስ ወንዝ ተነሥተው ወደ የመን አካባቢ ወደ ዘመዶቻቸው ሳባና ኤውላጥ ሸሹ። በመጨረሻም አለቃ ታዬተክለጻድቅ መኩርያና ሌሎች የኢትዮጵያ ጸሐፍት እንደመሠከሩ፣ ነገደ ኦፊር በኋላ በባብ ኤል መንደብ ተሻግረው በኩሽ መንግሥት ውስጥ በውጋዴን ሠፈሩ።

በልዩ ልዩ ዘመናዊ አስተሳስቦች፣ በአፍሪካ (ዚምባብዌሞዛምቢክ ወይም ኤርትራ)፣ ወይም በእስያ (አረቢያሕንድስሪ ላንካፊልፒንስ ወይም አውስትራሊያ) ወይም በደቡብ አሜሪካ (ፔሩ ወይም ብራዚል) እንደ ተገኘ የሚሉ ግመቶች ኖረዋል። የእስፓንያ መርከበኛ አልቫሮ ሜንዳኛ1560 ዓ.ም. በፓሲፊክ ውቅያኖስ ውስጥ የሰሎሞን ደሴቶች ባገኛቸው ጊዜ፣ ጥንታዊው ኦፊር እንደ ነበሩ ስላመነ ስማቸውን ሰጣቸው።