ቦሌ ዓለም አቀፍ ጥያራ ጣቢያ

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ የሚያገለግል አለም አቀፍ አየር ማረፊያ

ቦሌ ዓለም አቀፍ የጥያራ ጣቢያ (አውሮፕላን ማረፊያ)አዲስ አበባ ከተማ በደቡብ-ምሥራቅ አቅጣጫ ከአራዳ በስምንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ የአገሪቱ ዋና አድማሳዊ የንግድና የግንኙነት በር ነው።

የቀድሞው የበረራ ቁጥጥር እና መንገደኛ ማስተናገጂያ ሕንፃዎች
ቦሌ ዓለም አቀፍ የጥያራ ጣቢያ (አውሮፕላን ማረፊያ)
ቦሌ ዓለም አቀፍ የጥያራ ጣቢያ

ፕሮፌሶር (ዲባቶ) መስፍን አረጋ፣ ቦሌ በኦሮምኛ ቋንቋ ትርጉሙ የሚፈረፈር ወይም የሚሰነጣጠቅ መሬት እንደሆነ ይነግሩናል። እውነትም የአካባቢው ገጸ-ምድር ለአየር ማረፊያ አመቺ ሜዳማ ቢሆንም መሬቱ ግን ረግረጋማ እና መረሬ ነው።

በፋሺስት ኢጣልያ ዘመናት ለማስተካከል

ጥያራዎች (አየር ዠበቦች) ወደ አገሪቱ መግባት የጀመሩት በንግሥት ዘውዲቱ ዘመን ሲሆን በአዲስ አበባ ዙሪያ በጃን ሜዳ እና አቃቂ ያርፉ እንደነበር በታሪክ ተዘግቧል። የመጀመሪያው ቋሚ የጥያራ ጣቢያ ግን የተሠራው በአምሥቱ የፋሺስት የወረራ ዘመናት ሲሆን የካቲት ፳፬ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ/ም አክሱም አካባቢ ላይ ከነጥያራው ተከስክሶ በሞተው አብራሪያቸው፣ “ኢቮ ኦሊቬቲ” (Ivo Olivetti) ስም ሠይመውት የነበረው የልደታ የጥያራ ጣቢያ ነው።

በዚሁ በፋሺስት ወረራ ዘመን ‘አላ ሊቶሪያ’ (ALA LITTORIA S.A., R.) የተሰኘው ኩባንያ በአገር ውስጥ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ነገሌን፤ ሞቃዲሾን፤ ድሬዳዋን፤ ቆራኄን፤ ጂቡቲን፤ አሰብን፤ ጂማን፣ ጋምቤላደምቢዶሎን፤ ጎንደርን፣ አስመራን፤ ደሴን፤ ነቀምትን እና አሶሳን የሚያገለግሉ የበረራ መሥመሮች ሲኖረው ከአድማስ ባሻገር ደግሞ በካርቱም፣ ዋዲ ሃይፋ፤ ካይሮቤንጋዚ እና ሲራኩሳ አድርጎ ከሮማ ጋር የሚያገናኝ የበረራ መሥመርም ነበረው።

ከድል በኋላ ለማስተካከል

ከድል ወዲህ ልደታ ጥያራ ጣቢያ፤ የብሪታኒያ ጦር ኃይሎች ሲገለገሉበት ከቆየ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ታኅሣሥ ፳፩ ቀን ፲፱፻፴፰ ዓ.ም ሲመሠረት ዋና ጣቢያው እዚያው ነበር። ዳሩ ግን የአየር መንገዱ አገልግሎት እየተስፋፋ ሲመጣና ትላልቅ ጄት አውሮፕላኖች እንደሚያስፈልጉት ግልጽ ሲሆን፣ የልደታ አየር ጣቢያ ብቃት እንደሌለው እና ለጄት አየር ዠበቦችም ማሳረፊያ የማይስማማ መሆኑ ታምኖበት አማራጭ ሥፍራ ፍለጋ ተጀመረ። የአዲሱንም አየር ጣቢያ ዝርዝር ጥናት እንዲያዘጋጅ ውሉ ለአሜሪካዊው ‘አማን እና ዊትኒ’ (Amman, and Whitney) ኩባንያ ተሰጥቶ፤ ጥናቱ በ፲፱፻፶ ዓ.ም ተገባዶ አማራጩ ሥፍራ ቦሌ እንዲሆን ተወሰነ።

አዲሱ የጥያራ ጣቢያ ለማስተካከል

ቦሌ ሜዳማ አካባቢ ሲሆን፣ ለመነሳትም ሆነ ለማረፍ ከሚከለክሉ ተራራዎችና ጋራዎች የራቀ ሥፍራ ነው። የከተማዋም ወሰን በወቅቱ ከመስቀል አደባባይ እና ከኡራኤል በማያልፈት ጊዜ ለአየር ጣቢያው ቋሚነት የታጨው አካባቢ ከከተማ ውጭ እና ራቅ ያለ ነበር። የአየር ጣቢያው የግንባታ ወጪ ከአሜሪካዊው ‘ኤክስፖርት-ኢምፖርት’ ባንክ በተገኘ ብድር ተሸፍኖ ሥራው ተጀመረ።

የግንባታው ሥራ ጨርሶ ባይጠናቀቅም እንኳ፤ የማኮቦቢያው እና የበረራ ቁጥጥሩ ሕንፃ ሥራ እንደተገባደደ አየር መንገዱ የገዛቸውን ሁለት የጄት ዠበቦች (‘ቦይንግ ፯፻፯) ሲረከብ እዚሁ ቦሌ ጥያራ ጣቢያ ነበር ያረፉት። ጠቅላላ ግንባታው ተጠናቆ ሲያልቅ ኅዳር ፲፩ ቀን ፲፱፻፶፮ ዓ.ም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተብሎ፣ በንጉሠ ነገሥቱ ተመርቆ ተከፈተ።

እድሳት እና መስፋፋት ለማስተካከል

የየአዲሶቹ ጄት ጥያራዎች ክብደት፤ የአየር መንገዱ በረራ መሥመሮች መብዛት እና የማኮብኮቢያው መሠረት ግንባታ ጥንካሬ ወትሮውንም አስተማማኝ አለመሆን፤ የተነጠፈውም መረሬ እና የመሸርሸር ጠባይ ባለው አፈር ላይ በመሆኑ ከአምስት እና ስድስት ዓመታት አገልግሎት በኋላ የመሰነጣጠቅ ባህሪ ይታይበት ዠመር። ስለዚህ ማኮብኮቢያውን የማጠንከር እና ርዝመቱን በሰባት መቶ ሜትር የማራዘም ሥራ አዲስ በተገኘ ብድር ተጠናቋል።

የአገሪቱ የአየር ግልጋሎት እያደገ ሲሄድ መንገደኛ ማስተናገጃ ሕንፃዎቹም የግድ መስፋፋት እንደነበረባቸው ግልጽ ሲሆን ከጃፓን መንግሥት በተገኘ ብድር ተስፋፍቶ ኅዳር ፳፩ ቀን ፲፱፻፸ ዓ.ም ተመርቆ ተከፈተ።

ዋቢ ምንጮች ለማስተካከል

  • (እንግሊዝኛ) FO 371/178551 Annual Review of 1963

From Mr J W Russell – Addis Abeba to Mr Rab Butler (1st January, 1964) [1015/64]

Bole International Airport (ADD/HAAB), Addis Ababa, Ethiopia