ቅዱስ ራጉኤል

መጋቤ ብርሃናት


ራጉኤል ፣ በእንግሊዘኛ ሲፃፍ:Raguel ሲነበብ ‘’ራጉዌል’’; በግሪክ ሲፃፍ: Ῥαγουὴλ ሲነበብ:Rhagouḕl; በዕብራይስጥ ሲፃፍ: רְעוּאֵל ሲነበብ:Rəʿūʾēl እግዚአብሔርን ቃል አስከባሪ(የሕግ መላዕክ) ማለት ነው፡፡ የሰይጣናትን ጥፋት የሚበቀልም ነው.. . ፤ በብርሃናት ላይ የተሾመም መልአክ ነው ፤ በዚህም መጋቤ ብርሃን ይባላል፡፡ የወደቁ መላዕክትን ይቆጣጠራል፡፡ ይቀጥላል ራጉኤል ሊቀ መላእክት:- ራጉኤል ማለት የብርሃናት አለቃ ማለት ነው። የብርሃናት አለቃ ሲባል ፀሐይን፣ ጨረቃን እና ከዋክብትን በማመላለስና ለሰው ልጆች፣ ለአዝርዕት፣ ለእንስሳት፣ ለአራዊት ሁሉ ብርሃንን የሚመግብ ነው ማለት ነው። አንድም ራጉኤል ማለት የሚበቀል ማለት ነው። የሚበቀል ነው ማለት በቀል የሚገባው ለጠላት ነው የሰው ልጅ ጠላት ደግሞ ዲያብሎስ ነው፤ ስለሆነም ቅዱስ ራጉኤል እግዚአብሔርን አምነው ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀው በፍርሐተ እግዚአብሔር አምልኮቱን ለሚፈጽሙ ሁሉ ጠላት ዲያብሎስን የሚያርቅላቸው ወደ እነርሱም ፈጥኖ በመድረስ የሚታደጋቸው ነው ማለት ነው። ሔኖክ 6:4፡፡ አንድም ራጉኤል ማለት የኃያላን ኃያል እግዚአብሔር ማለት ነው። የኃያላን ኃያል ያለው የእግዚአብሔርን ኃያልነት ከምድር ፍጥረታት ዘንድ ኃያል ከሚባሉት ሁሉ ሊገለጽ የማይችል ኃያልነቱን ለመግለጽ ኃያልነቱም ከ እስከ የሌለው መሆኑን ለመግለጽ የተቀመጠ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር ኃያል የኃያላን ኃያል መሆኑን የሚገልጽ ትርጉም አለው። አንድም ራጉኤል ማለት ጽኑ እግዚአብሔር ማለት ነው። የእግዚአብሔር አምላክን ጽኑነት ለማጉላት ሲል ጽኑ አለው። እግዚአብሔር የማይወላውል የማይዋዥቅ የማይከዳ ነው ለማለትም ሲል ይህ ስያሜ ተሰጠው። የእግዚአብሔርን ጽናት የሚያሳይ ትርጉም ያለው ስያሜ ነው። የሊቀ መላእክት የቅዱስ ራጉኤል አገልግሎት እና ስልጣን፡- እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ ዓለም በ64 ዓመቷ ካረፈች በኋላ ሥጋዋ ወደ ዕፀ ሕይወት ሲነጠቅ (ሲያርፍ) አብሮ ለሔደው እና ስጋዋን በእጣን ሲያጥን ለነበረው ለፍቁረ እግዚ ለቅዱስ ዮሐንስ ኅብስትን የመገበ መልአክ ነው። በብርሃናት ሁሉ ላይ የሰለጠነ መልአክ ነው። ከአዳም ሰባተኛ ትውልድ የሆነ በእግዚአብሔር ፊት ግሩም ያማረ ሥራው የሰመረ እስከዛሬ የሞት ወጥመድ ያልያዘው የሞት ጥላ ያላረፈበት ነብዩ ሔኖክ "ከቅዱሳን መላእክት አንዱ የሆነ ጸላዒ ዲያብሎስን የሚበቀለው ራጉኤል በብርሃናት ላይ የሰለጠነ ነው" ሲል ስለ እርሱ ተናግሯል፡፡ እግዚአብሔር ዓለምን ይቆጣጠር ዘንድ የሾመው ታላቅና ቅዱስ መልአክ ነው። (ድርሳነ ራጉኤል ዘ ጥቅምት ገጽ 23) አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ለመተካት ዓለምን የመለወጥ ሥልጣን የተሰጠው ቅዱስ መልአክ ነው። ከእግዚአብሔር የጌትነቱ አዳራሽ ይገባና ይወጣ ዘንድ ስልጣን ያለው ከኪሩቤልና ከሱራፌል ጋር ከፈጣሪ የጌትነት ዙፋን ፊት የሚቆም ነው። ሎጥን ሚስቱንና ልጆቹን ከእሳተ ጎመራ ያዳነ የበለአምን እርግማን ወደ በረከት የለወጠ እርሱ ነው። በቅዱስ ራጉኤል ስነ ሥዕል ላይ የምናየው ይህ ባለ አራት እራስ ንስር ከአርባእቱ ኪሩቤል አንዱ ገጸ ንስር ነው። የሥላሴን የጌትነት ዙፋን የሚሸከሙ አርባዕቱ እንስሳት ናቸው። የሚሸከሙት ሲባል ጫማ የሰውን ልጅ እንደሚሸከመው እንጂ ችለውትስ አይደለም። እነርሱም የሰው ገጽ፣ የእንስሳ ገጽ፣ የንስር ገጽ እና የአንበሳ ገጽ ያላቸው ናቸው። ይህንንም ነብዩ ሕዝቅኤል "ለእያንዳንዱ እንስሳትም የተለያዩ አራት ገጾች ነበሩት። ይህውም በስተቀኝ በኩል የእንስሳ መልክ፣ በስተ ግራ የላም ገጽ፣ በበስተ ኋላም የንስር ገጽ የሚመስሉ ነበሩ" ብሏል ሕዝ 1፡6-13፡፡ ከዚህ የምንገነዘበው ነገር ቢኖር አራት ገጽ ካላቸው ኪሩቤል መካከል አንዱ ንስር መሆኑን ነው። ቅዱስ ራጉኤል ደግሞ የእነዚህ ኪሩቤል አለቃቸው (የጌትነቱ ዙፋን ጠባቂ) በመሆኑ በዚህ ምክንያት ማለትም እነርሱ ዙፋኑን ተሸካሚ እርሱ ደግሞ አጠገባቸው መቆሙ መንበሩን ጠባቂ በመሆኑ በዚህ አይነት የአገልግሎት ድርሻ አብረው ሊሳሉ ችለዋል። ቅዱስ ያሬድም በድጓው "አርባእቱ እንስሳ አልቄንጥሩ እንደሚባለው ንስር ፊት ለፊት አይታዩም አንዱም በመራቸው ይሔዳሉ እነርሱም እያንዳንዳቸው አራት ገጽ ሲኖራቸው ሳያርፉና ሳይደክሙ የሚያመሰግኑ ናቸው" በማለት ጽፏል። አንድም መላእክት ነገደ ሱራፌል እና ነገደ ኪሩቤል በመባል ይከፈላሉ። በነገደ ሱራፌል እነ ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ሩፋኤል ወዘተ ሲሆኑ በነገደ ኪሩቤል ደግሞ ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ራጉኤል ወዘተ ያጠቃልላል። ስለዚህ ቅዱስ ራጉኤል ነገዱ ከነገደ ኪሩቤል ነው በዚህም ላይ የነገደ ኪሩቤል አልቄንጡራ (አራት እራስ ንስር) አለቃቸው ቅዱስ ራጉኤል ነው። በዚህም ምክንያት አብረው ሊሳሉ ችሏል። አንድም መላእክትን ሁሉ እንደ እየስራቸው መለያ ስነ ሥዕላቸውን መሳል ልማድ ነውና። ለምሳሌ ቅዱስ ሚካኤል ከቅድስት አፎምያ ጋር፣ ቅዱስ ገብርኤል ከሠለስቱ ደቂቅ ጋር፣ ቅዱስ ዑራኤል ከእዝራ ሱቱኤል ጋር እንደሚሳሉት ሁሉ ማለት ነው። በዚህም መሰረት ቅዱስ ራጉኤልም ዐቃቤ መንበር ነውና መንበሩን በሚሸከሙት ኪሩቤል ከሚመሰሉት ንስሮች ጋር አብረው ሊሳሉ ችለዋል፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ራጉኤል ከአምላክ የተሰጠው ቃል ኪዳን እግዚአብሔር አምላክ በስሙ ለታመኑት ቅዱሳን፣ ጻድቃን፣ ሰማእታት፣ ሐዋርያት፣ ዘወትር ያለማቋረጥ ስሙን ለሚጠሩት ቅዱሳን መላእክት ሁሉ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል። የሰጣቸውም ቃል ኪዳን ዘላለማዊ እና ሊሻር የማይችል ነው። ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ራጉኤልም ይህን ቃል ኪዳን ሰጥቶታል "የራጉኤል አምላክ ይቅር በለኝ በማለት አንዲት ቃልስ እንኳን ቢናገር እንደ ወዳጄ እንደ አብርሃም፣ እንደ ባለሟሌም እንደ ይስሐቅ፣ እንደ አከበርኩትም እንደ ያዕቆብ ክብርን ባለሟልነትን እሰጠዋለሁ በራሱ ላይም አክሊል አቀዳጀዋለሁ እረጅም ዘመናት ሰፊ ወራትም እሰጠዋለሁ" ሲል ቃሉን ሰጥቶታል፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ራጉኤል መስከረም 1 ቀን ከሊቃነ መላእክት በ4ተኛ ደረጃ የተሾመበት ዕለት ነው። ግንቦት 1 ቀን ለታላቁ አባት ለሄኖክ ምሥጢራትን የገለጸበት በዓሉ ነው፡፡ ጥበቃው አይለየን፣ በምልጃው ይማረን፡፡ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ሀገራችንን ይጠብቅልን፡፡

ቅዱስ ራጉኤል
ሊቀ መላዕክት
ራጉኤል ማለት የኃያላን ኃያል የእግዚአብሔር ኃይል ምርት ነው
በየወሩ ታስቦ የሚውለው በወሩ መጀመሪያ ቀን ፩
የንግሥ ቀን መስከረም ፩
የሚከበረው በመላዕክት ተራዳኢነት በሚያምኑ ክርስቲያኖች
መዐረግ መጋቤ ብርሃናት